ጥቅምት 1 ቀን 2018ዓ.ም
ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከኩሪፍቱ አፍሪካ መንደር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች ፌስቲቫል <<የኢትዮጵያ ወር/Ethiopian Month>> በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መርሐ-ግብር ኢቱአባማ ተሳትፎ አድርጓል።
ዝግጅቱ እስከሚቀጥለው ህዳር የሚከበር እና የሚቆይ ሲሆን ፤ ኢትዮጵያን የሚወክል ማረፊያ ክፍል እና ባህላዊ ምግብ እና መጠጦች ለእይታ እና ለቅምሻ ቀርበውበታል።
በዝግጅቱ ላይ የማኅበራችን ዐዳዲስ አመራር አባላት በዋነኝነት የተሳተፉ ሲሆን ከተሳተፊ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እና ከመርሐ ግብሩ ተባባሪ አዘጋጅ ከኩሪፍቱ አፍሪካ መንደር ሥራ አመራር እና ባለቤቶች ጋር ዕድሉን በመጠቀም ትውውቅ አድርገዋል።
እንዲህ ያለ ፌስቲቫል በአንድ ቦታ ላይ መዘጋጀቱ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችን በማስተዋወቅ የምግብ ቱሪዝምን ከማሳደግ ባሻገር የሀገር ገጽታን ለመገንባት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ከመገንዘብ እና የመርሐ ግብሩን ቀጣይነት በመረዳት ፤ በዝግጅቱ ቢጨመሩ እና ቢሻሻሉ ብለን ያሰብናቸው ነገሮች
1. የተደረደሩ ምግቦችን በተመለከተ – ከምግቡ ስም እና የመጣበት አካባቢ ባሻገር አጫጭር መግለጫዎች ተፅፈው ቢለጠፉበት የምግቡን ምንነት በአጭሩ ለመረዳት ይጠቅማል
2. በመድረኩ ሙሉ የኢትዮጵያውያንን ምግብ ማቅረብ ባይቻልም ከወካይነት አንፃር የሚቀርቡ ምግቦችን በየሳምንቱም ሆነ ሌላ የቀናት ዙር ማቀያየር ቢቻል ውክልናን ከማስፋት አንፃር እጅግ ጠቃሚ ይሆናል
3. የመድረኩን ገፅታ ግንባታ ሚና ከማጉላት አንፃር ከኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች በተጨማሪ የውጭ ሀገር ታዳሚያንን በብዛት በተለይም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ማካተት ቢቻል ተደራሽነቱን ለማስፋት ያስችላል ብለን እናምናለን።
በአጠቃላይ የእንደዚህ አይነት መድረኮች መፈጠር የባለድርሻ አካላት የመገናኛ መድረክ ከመሆን ባለፈ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት እና የሃገር ውስጥ ባህላዊ ምግቦች ለዓለም ዓቀፍ ገበያ የሚቀርቡበትን መንገድ ማሳያ ከመሆን አንፃር ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ብለን እናምናለን።
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር